ዜናዎች | 09.01.2009 | 14:00 UTC
ናይሮቢ-የሳዑዲ አረቢያዋ መርከብ ተለቀቀች
የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ባለፈዉ ሕዳር አግተዋት የነበረችዉን የሳዑዲ አረቢያ ግዝፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ዛሬ መልቀቃቸዉን አስታወቁ።አግድም ሰወስት መቶ ሰላሳ-ሜትር የምትረዝመዉ ወይም ሰወስት የእግር ኳስ ሜዳ የምታክለዉ መርከብ ሥትታገት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነዳጅ ዘይት እንደጫነች ነዉ።ከአጋቾቹ አለቆች አንዱ መሐመድ ሰኢድ ዛሬ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደነገረዉ መርከቢቱ ከነ-ሰራተኞችዋ ቆማበት ከነበረዉ ሥፍራ ተንቀሳቅሳለች።መርከቢቱ ያሳፈረቻቸዉ ሃያ-አምስት ሠራተኞችዋም በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኙ የአጋቾቹ አለቃ ተናግሯል።አጋቾቹ መርከቢቱን የለቀቁት ገንዘብ ተከፍሏቸዉ እንደሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መናገራቸዉ አልቀረም። የተከፈላቸዉን ገንዘብ መጠን ግን አላስታወቁም።አንዳድ የዜና ምንጮች ለአጋቾቹ 3 ሚሊዮን ዶላር ቤዛ እንደተከፈላቸዉ ዘግበዋል።




